Skip to content

የት ሄዱ?!

ባንድ እነርሱ፥
— ብዙ —
እየተሸከሙ፣
ያደምቁኝ የነበር፣
ተስፋ ያለመልሙ፤
ዞር ባልኩኝ አፍታ፥
ባንጋጠጥኹኝ ቅፅበት፥
ካ’ይኔ ሲጋጠሙ፥
ያፍታቱኝ የነበር፥
ሀሴት ይቀምሙ፤
የብርሃን ቁሶች፣
የወጋገን ኳሶች…

ከሰማይ ተሰቅለው፥
ምሽቱን ያቀልሙ፣
ብትንትን ፈርጥ ሆነው፥
ውበት ይሸልሙ፤
ጨለማውን ሰማይ፥
ያሞግሱ፣ ያገርሙ፤
ምኞት ይቀምሩ፣
ተስፋን ይቀምሙ፣
የነበሩት ያኔ፥
የተስለመለሙ…
የብርሃን ነጠብጣብ፥
የተስፋ እንክብሎች
የት ሄዱ ከዋክብት?

ታነቃቃ የነበር፥
ታጃጅል የነበር፥
እያቁለጨለጨች…
የብርሃን ግንዲላ፥
በውብ ምሽት በቅላ፤
ያዙኝ ያዙኝ ‘ምትል፣
አውርዱኝ፣ አውርዱኝ፥
ብሉብኝ፣ ብሉብኝ፣
(ዋጡኝ ዋጡኝ፥ ወላ፥
ሰልቅጡኝ፣ ሰልቅጡኝ)
የምትል የነበር…
የወጋገን ግግር፣
የብርሃን ትሪ፥
ከሰማይ ተሰቅላ፥
ተስፋን ታለመልም፣
ባዶውን ትሞላ፤
የነበረች ያኔ፥
ስጋ ትቀባባ፥
ኩስምንምኑን ገላ፤
ሞጌ ጉንጩን ሁላ፥
ድንቡሽቡሽ ታስመስል፣
ፈገግታ ደልድላ፤
ታስውብ የነበረች፥
ዳፍንታሙን አየር፥
ብቅ ባለች ቅፅበት፥
ታፍመው የነበር፣
ታቀላ እንዳለላ፤
የት ሄደች ጨረቃ?

እ’ሷ ስታረፍድ፥
ከዋክብት ሲቀሩ፥
ብቅ ይሉ የነበር፣
ደስታ ይቆሰቁሱ፣
ሳቅ ይወተውቱ፣
ተስፋን ያነቃቁ፥
እምነትን ያደምቁ፥
ያጫውቱ የነበር፥
ካ’ሳብ ያናጥቡ፣
ኦናን ያዋክቡ፥
ድብርት ያጣጥቡ፣
ያጓጉ የነበር፥
የት ሄዱ አብሪ ትሎች?

ቅርንጫፎቻቸው፣
እርስ በ’ርስ ሲጋጩ፥
ሲያረግዱ፣ ሲንሿሹ፤
ንፋስ እያፏጨ፥
ሲገፋቸው ጊዜ፣
ደርሰው ሲወራጩ፣
እዚህ እዚያ ሲነኩ፥
ከብበው ሲፈነጩ፥
ያበሩ ይመስለኝ፥
የነበረው ያኔ፣
የት ሄዱ ዛፎቹ?

ቀን ሲመሽ ጠብቆ፥
ምሽቱ የጠመመ፣
ተደቅድቆ ጠቁሮ፥
ሰማይ የፀለመ፥
ሳቅ፣ ተስፋ የራቁ፥
እምነት የዘመመ፣
አልጋ እግሩ የዛለ፥
እንቅልፍ የታመመ፣
እረፍት የደከመ፣
ከቶ ለምን ይሆን?
ድፍንፍን ማለቱ፥
ከሌላ ተስማምተው፥
ከሌላ ተዋድድደው፣
ጨልሞ ሊቀር ነው?
የሚነግረኝ ማነው?
ከጊዜ በስተቀር፥
የሚያሳየኝ ማነው?

ብቻ ግን…
ይኽ ምሽት ካለፈ፥
ሌ’ቱ ከተገፋ፣
ፅልመት ከረገፈ፣
እንደምንም ብሎ፥
አንድ’ዜ ከነጋ፥
ዳግም አይጨልምም፣
ብርሃን ትቆማለች፥
(ብትፈልግ ከሰማይ—
እልም ስልም ትበል)
አትጠፋም ደጄ ጋ፥
አትጠልቅም ከእኔ አልጋ!

/ዮሐንስ ሞላ/

“ሰዶ ማሳደድ ካማረህ…”

“መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣1233402_436151109839261_1389450980_n
እንኳን ሰው ዘመዱን፣ ይጠይቃል ባዳ።”

ልጅ ሳለን ቢሆን ኖሮ፥ ይህኔ ወንዶቹ “አበባ” ስለን እንኳን አደረሳችሁ ብለን ከዘመድ ጎረቤት ቤት የሰበሰብነውን ፍራንክ እያሰብን፤ ሴቶቹም “አበባዮሽ” ጨፍረው ያገኙትን ሽልማት ሳንቲም እያብሰለሰሉ፣ እንቅልፍ አይወስደንም ነበር።

የበዓል ዋዜማው የፎርም (አበባ) ቆጠራ እና የገቢ ቅድመ ስሌት ቀን ነው። ከሰሞኑ በቀለም የተጨማለቀው እጅም በዚህ ቀን ተፈቅፍቆም ቢሆን ይጠራል። ከዚያ ሲነጋ፥ በየጎረቤትና ዘመድ ቤት “እንኳን አደረሳችሁ” እየተባለ አበባ ይሰጣል። ቀኑ ረፍዶ ረስተን አበባ ያልወሰድንባቸው ቤት እማወራ/አባወራዎች ‘ለምን አበባ አላመጣህም?’ ብለው እንዳይቆጡን ስለምንፈራ የምንሄድበትን ቤት ዝርዝር ቀድመን አዘጋጅተን፥ አበባውንም ቆጥረን ነው የምናዘጋጀው።
…ቤትም፥ “ኧከሌ ቤት ውሰዱ” እያሉ የረሳነውን ያስታውሱን ነበር። ሴቶቹም አዲስ የተገዛላቸውን ልብስ በዋዜማው ለብሰው “አበባዮሽ” እያሉ በየቤተዘመዱና ጎረቤቱ ቤት እየዞሩ ይጨፍሩ ነበር።

ነበር….!?

በርግጥ አበባዮሽ የሚጨፍሩ ጥቂት ልጆች ዛሬም ይታያሉ። ለዛና አጨፋፈሩ ግን እየተበላሸ እየተበላሸ፣ ስሜቱም እየቀዘቀዘ፣ እየቀዘቀዘ ነው የመጣው። ሰዉም ለልጆቹ የሚሰጠው ምላሽ፥ ነገሩን ከልመና ጋር እያቀራረበው የሚያሳፍራቸውም ይመስለኛል። ….አበባ የሚስሉ ጥቂት ልጆችም እንዳሉ ዛሬ ቤት ሲመጡ ተመልክቻለሁ። – ምናልባት ከቤቶቻቸው ተደብቀው?!

ሆኖም ግን ዘመናዊ (ነን ባይ) ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲህ ባሉ የበዓል እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅዱ አይመስለኝም። ከማጣትና ከመሳጣት ጋር ሲያገናኙት ይስተዋላል። ነገር ግን፥ በዓልና ባህል ከማግኘትና ከማጣት ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር ስለሌለ፥ ከማሸማቀቅና ከመከልከል ይልቅ ሊያበረታቷቸው ይገባል። አበባ ሲስሉ ቀለም እናቀብላቸው…. አበባዮሽ ሲሉ ትክክለኛውን ዜማ እናስተላልፍላቸው….

“ሰዶ ማሳደድ ካማረህ፥ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” ይባላል፥… እናም፥ ኋላ ማሳደዱ እንዳያደክመን፥ ባህሎቻችን እንዳይጠፉ እንንከባከብ። ከትውልድ ትውልድ፥ ከነሙሉ መልካቸው ስለመዝለቃቸው እንምከር።

ሸጋ እንቁጣጣሽ አሳለፍን!

ወዳጄ ወዳጄ የምንባባልበት፣ እርስበርስ በመመካከርና በመከባበር የምናፈራበት ዓመት ይሁንልን።

አሜን!

ስለ ረ/አብራሪው ኃይለመድኅን እና ስለተወሩ መላምቶች…

ስጀምር

ባለፈው ሰኞ፥ የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ/ም፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነች et702hijack_coverአውሮፕላን (ET 702) መድረሻዋ ሮም ሳለ፥ ኃይለመድኅን አበራ በተባለ የ31 ዓመት ወጣት የገዛ ረዳት አብራሪዋ ተጠልፋ ጄኔቭ ማረፏን ተከትሎ፥ ብዙ ዓይነት መላምቶችንና ያልተጣሩ ሹክሹክታዎችን ስንሰማ ቆይተናል። ሁሉም በየራሱ፥ ነገሩን ለማወቅ በመጓጓትና በሁኔታው በመደናገጥ፤ እንዲሁም ነገሩን በማለባበስና በጉዳዩ ለማትረፍ በማሰብ መካከል ሆኖ፥ …እውነቱን ከባለቤቱና ከምርመራው ውጤት እስኪሰማ ድረስ፥ ሥራም እንዳይፈታ፥… ‘ይሆናል’ ብሎ የገመተውን ለመግለፅና በመረዳቱ ልክ ጉዳዩን ለመተንተን ቢሞክርም፥ ማሰሪያው ዞሮ ድፍን ያለ ነገር ነው።

የኃይለመድኅን ዓላማና ፍላጎት ጥገኝነት መጠየቅና ማግኘት ብቻ ቢሆን ኖሮ፥ እንዲህ ያለውን ውስብስብና ጉዳት የበዛበት መንገድ ሳይመርጥ፣ እርሱም አደጋ ላይ ሳይወድቅ፣ ወገኖቹን ሳያስጨንቅና ሳያሳቅቅ፣ መስሪያ ቤቱንም ሳያሸማቅቅ በራሱ መንገድ ሊያደርገው እንደሚችልና ያንን ለማድረግ ሁኔታዎችን በራሱ ማመቻቸት እንደሚችል ግን ማንም ካለአስረጅ እንደሚገነዘብ አምናለሁ። ሌሎች ሁኔታዎች ከግምት ሳይገቡ እንኳን፥ በሰላሙ ጊዜና (under normal condition) ካለምንም የተለየ ምክንያት እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እንደማይገደድ ለመረዳት፥ ለአውሮፕላን አብራሪነት ያበቃውን የማሰላሰል ብቃቱን (analytical ability) መገመት በራሱ በቂ ይመስለኛል።

«ያውራ የነበረ…!»

አውሮፕላኑ ጄኔቫ ባረፈበት ወቅት ረዳት አብራሪው ለስዊስ ፖሊስ የሰጠው ቃል ሀገሩ ውስጥ ለመኖር ስጋት ስላለበት፥ የስዊዘርላንድ መንግስት ጥገኝነት እንዲሰጠው መፈለጉን የሚገልፅ ብቻ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ፥ እዚያ አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍሮ የነበረ ምህረቱ ገብሬ የተባለ ወጣት፥ በግል የፌስቡክ ገፁ ላይ ረዳት አብራሪው ኃይለመድኅን፥

Sit down Sit down…I am going to give u more oxygen,….sit down….we are on high altitude…

ሲል እንደነበርና፥ በአማርኛ ጭምር፥ “ዛሬ አምላክ ብቻ ነው የሚያድናችሁ” በማለት አጠቃላይ ሁኔታውን ገልፆ መፃፉን ከወዳጅ ተረድቻለሁ። (ለጊዜው ከፌስቡክ በመራቄ ራሴ አንብቤ አላረጋገጥኩም።) Redditor OK3n የተባለ/ች የ25 ዓመት ወጣት ተሳፋሪ፥

Everybody looked at each other, thinking what’s going on. Suddenly, a deep and angry voice talked through the cabin radio: “SIT DOWN, PUT YOUR MASKS ON, I’M CUTTING THE OXYGEN”, three times

በማለት ሁኔታውን ገልጿል/ለች። (ሙሉውን ከዚህ ያንብቡ)

ትንሳኤ vs ዓለሙ/ እህት vs አጎት

ከዚህ ውጭ የኃይለመድኅን ቤተሰቦችን በማነጋገር ረገድ፥ ከጉዳዩ ዓይነት (sensitivity of the issue) የተነሳ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ተገልጿል ቢባልም፥ እህቱ እና አጎቱ (በበኩሌ፥ እውነተኛ ዝምድናቸው ላይ ጠበቅ ያለ ጥያቄ አለኝ…) ገደምዳሜው አንድ ሆኖ እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተያየት ሰጥተዋል። – እህቱ ትንሳኤ አበራ በፌስቡክ ገጿ ላይ። (ከፌስቡክ ገጿ ላይ እንዳገኙት ገልፀው ካጋሩት ጦማሮች እንዳነበብኩት) አጎቱ ዓለሙ አስማማው ደግሞ ለAssociated Press (እዚህ ይመልከቱ). እህቱ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እንደመንስኤ የጠቀሰችው ሁኔታ ባይኖርም፥ አጎቱ መንስኤው የሌላ አጎቱ ድንገተኛ ሞት መሆኑን ለወሬ አውታሩ ገልፀዋል።

የትንሳኤ ገለፃ የሚያጠነጥነው የወንድሟ የአእምሮ ጤና ችግር ተጠቂነትን በመግለፅና እርሱን ለማሳመን በመሞከር ነው። እንዲህ ትላለች…. (ሙሉውን ለማንበብ)

ሃይለመድህን ሁሉንም አስታዋሽ ቤተሰቡን የሚወድና ተጫዋች ሰው ነበር እስከ ቅርብ ጊዜ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለኛ ያለውን ፍቅር ደህነታችንን በማረጋገጥና የሚያስፈልገንን ሁሉ በመታዘዝ ቢገልጽም ከዘመድ ወዳጆቹ ጋር መገናኘትና አቆመ። የወትሮው ጨዋታና ደስተኝነቱ ቀርቶ ብቸኝነትን የሚወድ ዝምተኛ ሆነ። ህይወቱ ደስታ የራቀው መሰለ። በሁኔታው ተደናግጠን ደጋግመን በመጠየቅ ያወቅነው ሊያጠቁት የሚከታተሉት ጠላቶች እንዳሉ እንደሚያምን ነው። ስልኩን እንደጠለፉት ያስባል፤ በላፕቶፑ ካሜራ ሳይቀር ያዩኛል ብሎ ስለሚሰጋ ካሜራውን ሳይሸፍን አይከፍተውም፤ ወጥቶ እስኪገባ ቤቱን ሲበረብሩ የቆዩ ስለሚመስለው ካሜራ ጠምዶ መሄድ ሁሉ ጀምሮ ነበር። ባጠቃላይ በታላቅ የመንፈስ ጭንቀት እየተሰቃየ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን ጉዳቱን ለኛ ለቤተሰቡንኳ አብራርቶ አለመናገሩ ነው። ወንድሜ ለሰዎች እርዳታ ለመድረስና የሌሎች አዳኝ ለመሆን የማይታክት ሰውንጂ እንዲህ በሚያንገበግብ ስቃይ ውስጥንኳ ለራሱ አስቦ እርዳታን የሚጠይቅ ሰው አይደለም። ሁኔታውን በደበስባሳው በታወቀበት ጊዜንኳ የሚያስፈልገውን የህክምና በማቅረብ ስላልረዳነው ቤተሰቡ ሁሉ እንደግር ሳት ይከነክነዋል።እሱ ግን እንዲህ ባለ ጥልቅ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥንኳ ለኛ አንድም ቀን ሳያስብ ቀርቶ አያውቅም።

Really?

ወረድ ብላም….

በኛ አገር መስሪያ ቤቶች የሰዎችን እውቀት ብቃትና ቁመና ሳይቀር ሲመዝኑ የዐይምሮ ጤንነት ሁኔታን አለመከታተላቸው እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው።

በማለት ዛሬ በልበ ሙሉነት ለመተንተንና ለማስረዳት እስኪያስችላት ድረስ፥ በወንድሟ ጤና ዙሪያ ላይ በቂ ግንዛቤ እንደነበራት የምትገልፀው እህቱ፥ ወንድሟ አስፈላጊውን ህክምና አግኝቶ ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ እንደመርዳት፥ ‘ሥራ’ ብሎ ሲሄድ ዝም ብላ ስትመለከት ኖራና፥… ሊፈጠርበት ስለሚችለው ጉዳይ ሳትጨነቅ [ችግሩ የአእምሮ ሁከት ከሆነ፥ ከቤት ወጥቶ ስራ ወይንም ርቆ ባህር አቋርጦ ሲሄድ ሊደርስ የሚችልበትን ቀውስ (crises) በመገመት ስለህክምናው መምከር፤… ‘ያምናል’ እንዳለችውም፥ የእውነት ሰዎች ሊያጠቁት ይከታተሉት ከነበረም ሊደርስ የሚችልበትን አካላዊ ጥቃት በማሰብ ቀድማ ለማስቀረት መመካከር ስትችል] ችላ ብላው ኖራ፥… ዛሬ ጣቷን ቀጣሪ ድርጅቱ ላይ ትቀስራለች። አሳዛኝነቱንም አበክራ ትናገራለች።

ይሄ ለእኔ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ትናንትና ችግሩን ይህን ያህል አስረድቷትና ተገንዝባ ከነበረችና ወደ ሆስፒታል ወስዳ ልትረዳው ካልቻለች እህት፥ ዛሬ ላይ ቢበዛ ከፍተኛ የሆነ ፀፀት ይጠበቅ ይሆናል እንጂ፥ እርሱን ሞያ እንደሰራ ሰው ስትተነትን መመልከት የምር ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ደግሞም ነገሩን ይበልጥ አሳማኝ ልታደርገው ስትል…

በተስተካከለ የዐይምሮ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሰው ላይገባው ይችላል። እኔ ግን የሱን ግማሽ ባያክልም የተወሰነ ይህንን መሰል ችግር ስላለብኝ ህመሙን አውቀዋለሁ።

ትላለች። ይህኔ ነው ግራ መጋባቴ ስር ሰድዶ፥ “የምር እህቱ ነች?” የሚል ጥያቄዬን አነሳ ዘንድ ያስገደደኝ። ጥርጣሬ ውስጥ የከተተኝ። ሲጀመር፥ “የርሱን ግማሽ ባያክልም” ብሎ ለመናገር መለኪያዋ ምን ሆኖ ነው? “ይህንን መሰል ችግር ስላለብኝ ህመሙን አውቀዋለሁ” አባባሏስ፥ ችግር አለ ብላ የጠቀሰችውን ቤተሰባዊ (hereditary) ለማድረግ ነውን? እንደዚያ ከሆነስ እንደምን ተረጋግታ ስለጉዳዩ ማስረዳት ቻለች? እንደምንስ 5 ዓመታት ውስጥ ያልተገለጠ ባህርይ ሆኖ ሊኖር ቻለ? ይህንንም እንተወው…. ምናልባት የወሬ ምንጮች ካልዘባረቁ በቀር፥ ስለ ኃይለመድኅን ቤተሰብ እንደተረዳሁት፥ ቤተሰቡ ውስጥ ሁለት የህክምና ዶክተሮች መኖራቸውን ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ጭንቀት ሊከሰትና በቀላል ህክምና ሊወገድ እንደሚችል ሲያውቁ፥ እንደምን የጤንነቱን ጉዳይ ችላ ሊሉት ቻሉ? ብዙ ግራ መጋባት…

ትንሳኤ ጭንቀት አለበት ማለቷን ድፍን ያለ ነው ያደረገችው። የጭንቀቱ መንስሄ የቅርብ ቤተሰብ ሞት መሆኑን ለመግለፅና መረጃ ለመስጠትም ከአጎት በቀረበ ባይሆን እንኳን፥ ቢያንስ ከአጎት እኩል መገንዘብ እንደምትችል አስባለሁ። ታዲያ ግን አጎቷ አቶ ዓለሙ፥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር በነበሩ እምሩ ስዩም በተባሉ ሌላ አጎቱ ድንገተኛ ሞት ምክንያት ኃይለመድኅን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ነው የገለፁት።

Schizophrenia? Depression? Or what?

በእኔ ጥቂት መረዳት፣ ልምድና፥ በጉዳዩ ላይ ቀደም ያለ ምክንያታዊ ንባብ (previous purposive reading on the topic)፥ እህቱ ከተነተነቻቸው ምልክቶች ተነስቼ፥ ችግሩ schizophrenia ሲመስለኝ፥ ደግሞ የአጎቱን ትንታኔ ስመለከት depression ይመስለኛል። (የህክምና ባለሞያዎች በዚህ ላይ ያለንን ግንዛቤ ትክክለኛ ለማድረግ ይረዱን ይሆናል) የሆነው ሆኖ፥ ሁለቱም የአእምሮ መታወኮች በስነ አእምሮ ባለሞያዎች በሚደረግ ክሊኒካዊ ምልክቶችን የመመርመር ዘዴ እንጂ፥ በአካላዊም ሆነ የናሙና ምርመራ መንገድ የላቸውምና፥ ሰው በዘፈቀደ እርስበርሱ ሲፈራረጅ ማየት አዲስ አይደለም።

በትንሳኤ መንገድ ሄጄ እንደተረዳሁት፥ የረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን ችግር ሺዞፎርኒያ ቢሆን ኖሮ በሁኔታዎች መጠርጠር ይቻላልና፥ ከርሷ በተጨማሪ ምልክቶቹን የስራ ባልደረቦቹና የቅርብ ወዳጆቹም ሊያዩት ይችሉ ነበር። ደግሞም እዚህ ጋር የምናምነው ሀቅ፥ ማናችንም ብንሆን፥ ስራ ፈት ካልሆንን በቀር፥ ቤት ውስጥ ከምናሳልፈው ጊዜ የበለጠውን ስራ ቦታ ነው የምናሳልፈውና የየዕለት ለውጦቻችንን ለመገንዘብ የስራ ባልደረቦቻችንም ሩቅ አይሆኑም። (ቤት ውስጥ የምናሳልፈው የእንቅልፍ ጊዜንም ይጨምራልና፤ እንዲሁም፥ ኃይለመድኅን ብቻውን ነውና የሚኖረው፥ ሲመስለኝ የስራ ባልደረቦቹ ከእህቱ ሰፋ ላለ ጊዜ ሊያገኙት ይችላሉ።)

እናም ወንድም ኃይለመድኅንን ሺዞፎርኒክ ነው ከተባለ፥ ማንም በሁኔታው ለውጡን ሊገነዘበው ይችላልና፥ መስሪያ ቤትም ቢሆን፥ ለእርሱ ቢቀር ለንብረትና ለደንበኞች በማሰብ እረፍት እንዲወስድ ያመቻቹለት ነበር እንጂ፥ መደበኛ ስራው ላይ እንዲሰማራ ይፈቅዱለታል ብዬ አላስብም። (“ካላበደ በቀር ዱባ ቅል አይጥልም።” ይባላል። እናም ማንም እንዲህ ዓይነት ችግር አይቶ ችላ ቢል፥ የዱባ ተክል ቅል ቢጥል እንዳለ እብደት ነው።) በዚህ በኩል፥ ወዳጆቹ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበረበት ገለፁ መባሉን አንብበናል። የአጎቱ ልጅ ነኝ ያለች ሴት ደግሞ፥ በኢሳት ቴሌቪዥን የስልክ ቃለ ምልልስ ላይ፥ “የሀገሪቱን ችግር ለህዝቡ ለማሳወቅ ፈልጎ ነው ይህን ያደረገው።” የሚል መልእክት አስተላልፋለች። (ለማድመጥ)

በአጋጣሚ ሆኖ፥ ብዙ ሺዞፎርኒክ ሰዎች አጋጥመውኝ ያውቃሉ። ሳይንሳዊ ትንታኔ ይኑረው አይኑረው ባላውቅም፥ ተደጋግሞ ከገጠመኝ በመነሳት፥ የሺዞፎርኒክነት ባህርይ አንዱ አለማስመሰልና ሀቀኝነት መስሎ ይሰማኛል። ሺዞፎርኒክ ሰው ራሱን ከማዳመጥና በገባበት ዓለም ከመመላለስ በቀር አይሞቀውም አይበርደውም ብዬ አስባለሁ። ስለሆነም፥ አውሮፕላኑን ወደ ጄኔቫ ጠልፎት ሲሄድ ለሺዞፎርኒክ ተጠቂ ትክክለኛ እርምጃና ስራ ነውና፥ ለማስፈራራትና ጥፋት እንደሚደርስ ተገንዝቦ “ዛሬ አምላክ ብቻ ነው የሚያድናችሁ” የሚል አይመስለኝም። እንደዚያ ካለ ከቀልቡ ሆኖ የሚሰራውንም ያውቃልና የአእምሮ መታወክ ችግር አለበት ማለት ይከብዳል።

Sign and symptoms of schizophrenia

Schizophrenia.com

People diagnosed with schizophrenia usually experience a combination of positive (i.e. hallucinations, delusions, racing thoughts), negative (i.e. apathy, lack of emotion, poor or nonexistant social functioning), and cognitive (disorganized thoughts, difficulty concentrating and/or following instructions, difficulty completing tasks, memory problems).

በማለት የሺዞፎርኒያ ህመም ምልክቶችን በደምሳሳው ያስቀምጣቸውና፥

Please refer to the information available on this page (see below) for common signs and symptoms, as well as consumer/family stories of how they identified schizophrenia in their own experiences.

በማለት ለበለጠ ንባብና ትንታኔ ይጋብዛል። እኔም ለጠቅላላ ግንዛቤም ሊረዳን ስለሚችል፥ የሚችል ያነባቸው ዘንድ እጋብዛለሁ።

Sign and symptoms of Depression

እንዲሁም በአጎቱ የገለፃ መስመር ሄደን፥ የኃይለመድኅን ችግር ዲፕረሽን ነው ብንል፥ ከሺዞፎርኒያ በላቀ መልኩ በቀላሉ ተለይቶ ሊታወቅ የሚችል ነገር ነው።

Beyondblue ገፅ

A person may be depressed if, for more than two weeks, he or she has felt sad, down or miserable most of the time or has lost interest or pleasure in usual activities, and has also experienced several of the signs and symptoms across at least three of the categories below.

ብሎ የዲፕረሽን ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን behaviour, feelings, thoughts, እና physical በማለት በየመደቡ አስቀምጧቸው ምልክቶቹን ይዘረዝራል። (read more)

እናም ከምልክቶቹ እንደምንረዳው ዲፕረሽን ውስጥ ያለ ሰው ከሺዞፎርኒያም ጋር ሲነፃፀር በቀላሉ ታይቶም ሊታወቅ የሚችልበት ሁኔታም ጭምር መኖሩን ነውና፥ ኃይለ መድኅን እንደዚያ ዓይነት ችግር ቢኖርበት ኖሮ ከቤተሰቡ ባልተናነሰ በስራ ባልደረቦቹም መታወቁ አይቀርም ነበር ይመስለኛል። ያንን እያወቁ ስራ ላይ ካሰማሩት አሁንም “ካላበደ በቀር ዱባ ቅል አይጥልም።” እንጂ ሌላ ምን ማለት ይቻላል?

አየር መንገዳችን – እንደመደምደሚያ!

አየር መንገዳችን ብዙዎች እንደ ብርቅ የምንንከባከበውና የምንኮራበት ሀገራዊ ንብረታችን ነው። ከነድክመቱም፥ በነገሮች አንገታችንን በደፋንና በተሸማቀቅንባቸው ጊዜያት፥ ልክ እንደ አትሌቶቻችንና የድል ታሪኮቻችን አንገታችንን ቀና ያደረገልንና ዛሬም ደረታችንን የሚያስገለብጠን ባለውለታችን ነው። …ከተሳፈረበት አንስቶ፥ እንደ አሞራ ሰማይ ላይ ብቻ እስከሚመለከተው ኗሪ ድረስ፣ የአውሮፕላናችንን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ሰንደቅ አላማ ሲያይ ልቡ ወከክ የማይል የሚኖር አይመስለኝም። በልጅነት እንኳን የአውሮፕላን ድምፅ ስንሰማና በእኛ መኖሪያ አካባቢ ሰማይ ላይ ሲያልፍ፥ እጅ ነስተን “አባባባባባ….” በማለት መዳፋችንን አፋችን ላይ እያገጫጨን ነበር የምናሳልፈው። ሌላም ሰፈር እንዲሁ ነበር ይመስለኛል።

እናም አካሄዳችን ይለያይ እንደሆን እንጂ ማንኛውም የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለው ሰው ለአየር መንገዳችን ደህንነትና ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት መጨነቁ አይቀርም። ስለሆነም፥ ኃይለመድኅን ድርጊቱን የፈፀመው የአእምሮ ሁከት ስላለበት ነው ማለቱ ለአየር መንገዳችን ስምና ዝናም መልካም የሚሆን አይመስለኝምና፥ ቢያንስ ጉዳዩን ከባለቤቱ እስክንሰማ ድረስ መላምቶቻችንን በኃላፊነት ብንሰነዝር መልካም ይመስለኛል። በዚያም ላይ ኃይለመድኅን አሁን ያለበትን ሁኔታ ማንም አያውቅምና ዛሬ የምንናገረው ነገር ጉዳዩን በማጦዝና በማሾር ረገድ የሚጫወተውን ሚና ላናውቅም እንችላለንና ነገሩ እስኪጠራ ድረስ ዝም ብንል የተሻለ ይመስለኛል።

እስከዚያው ድረስም ግን፥ አየር መንገዳችን የሁላችንም ኩራት ሆኖ እንዲዘልቅ፥ በፓርቲ መቀያየርና በመንግስት መለዋወጥ ማዕበሎችም ጭምር እንዳሸበረቀና እንዳኮራን እንዲኖር የአስተዳደር ቦርዱ ውስጡን በመፈተሽ እንደ ላዩ ያማረ አሰራር ስለማበጀት ቢመክር ጥሩ መሆኑ አይጠረጠርም። አዎ! የአየር መንገዳችንን ስኬት እንደምንጋራና እንደምናደንቅ ሁሉ፥ መጥፎ ነገሩንም አንፈልግምና ኃላፊዎች ያስቡበት ዘንድ ይገባል።

ቸር ቸሩን ያሰማንማ!

አልወዳለሁ!

ንፋስ እወዳለሁ፤…
ንፋስ ማን ይጠላል?images
ከገለባ ጋራ መውደድ እንዳይደረጅ
የበራሮች ፍቅር እንዳያንቦጃቡጅ፥
እንዳያንጎላጅጅ፣
እንዳያሳር እግር፣ እጅ፤
በጊዜ ጠራርጎ ይወለውልና፥
ብርቱውን ያስቀራል፤
አቁሽሹን አብርሮ፥
ቋሚውን ያስበራል፤
አፍዝዙን ወልውሎ፥
ጥንኩሩን ያደምቃል።
ንፋስ ማን ይጠላል?!

ንፋስ እጠላለሁ፤…
ንፋስ ማን ይወዳል?
ገለባ፣ ልጣጩን፣ ጥራጊውን ሁሉ፥
ኬ’ትም ደጃፍ ዘግኖ፥
ኬ’ትም ሰፈር ለቅሞ፥04a227964828823e18db88ce9e1b7247
ሰውነት ላይ ጭኖ፥
ገላን አሸክሞ፥
ብርቱን ያቆሽሻል፥
ደማቁን አዳክሞ፤
መልኩን ይጋርዳል፥
ብርሃኑን ጨላልሞ።
ንፋስ ማን ይወዳል?!

ሲበሩ፣ ሲያበሩ፥
ተገትሬ ቁሜ እቀዣበራለሁ፥
ንፋስ አልወዳለሁ።

/ዮሐንስ ሞላ/

Note: Photos are found from internet.

‘Eske Meche’ – Gigi (Ejigayehu Shibabaw)

Eske meche

This post is dedicated to Yohanes Molla from Ethiopia, who was the 300th person who liked JUSI I LOVE on Facebook. Since I offered the 300th person to choose any song I would later post about, he stated the wish to have a post about a song by Ejigayehu Shibabaw. Check out Yohannes Molla’s page (Chocolate porch) here.

Born and raised in Chagni in northwestern Ethiopia, Ejigayehu Shibabaw, popularly known as Gigi, has become one of Ethiopia’s best known singers. The track ‘Eske Meche‘ (Until When) is taken from her LP ‘One Ethiopia‘, which is only one of seven great albums the Ethiopian singer has produced so far, the latest being ‘Mesgana Ethiopia‘. Although she is famous for fusing contemporary and traditional sounds, her sound is clearly rooted in Ethiopian popular music.

‘Eske Meche’ – Gigi (Ejigayehu Shibabaw).

ትንሽ ሂሳብ – ስለ ቦይኮት በደሌ!

የፌስቡክ ግሩፕ ውስጥ፥ ሰዎች ፈልገው ብቻ ሳይሆን ግሩፑ ውስጥ ባሉ አባላቶች add ስለሚደረጉ (ወደ ግሩፑ ስለሚገቡ) …አባል የሆኑት፥ በትክክል አምነውትና ጉዳዩን ለይተውት ይሁን፥ ዝም ብለው ወደ ግሩፑ ስለገቡ፥… ምንም አይታወቅም።

ቀላል የሂሳብ ምሳሌ፥… Jawar Mohammed 5000 ጓደኞቹን፣ Daniel Berhane እንዲሁ 5000 ጓደኞቹን፣ Alula Solomon እና Abiy Atomssaም ጓደኞቻቸውን፥ ሌሎች አራጋቢዎችና ጠብ አጫሪዎችም እንዲሁ ያሏቸውን ጓደኞች ሰብስበው ቢያዋጡ፥ ግሩፑ በተከፈተ 1 ሳምንት አይደለም፥ …የinternet ኮኔክሽን ችግር ካልገጠመ በቀር፥ በተከፈተ በአንድ ቀኑም 37, 000 አባላት ሊኖሩት ይችላሉ።

ስለሆነም፥ የፌስቡክ ግሩፕ አባላት ብዛት፥ ስለ ግሩፑ ጥንካሬና ወደው ስለሚከተሉት አባላቶቹ የሚነግረን አንዳችም ነገር የለውም። ይሄ “…በምርጫም ሆነ በአማራጭ ማጣት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ90 ሚሊየን በላይ ብዛት ያለው ሕዝብ፥ ኢህአዴግ በሚያስተዳድረው ግዛት ውስጥ ስለሚኖር፣ የመንግስት ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ስለሆነና፥ ሀገር ውስጥ ሰርቶ ለመንግስት ግብር ስለሚከፍል፥ የመንግስት ወዳጅና ደጋፊ ነው።…” ብሎ ከመደምደምና ሰዎችን ከማደናገር ያልተናነሰ ውስልትና ነው። ….እንዲህ ባለ ሂሳብ ሰውን ለማታለልና ጆሮ ፍለጋ ማባበልም «እቆረቆርልሀለሁ፤ ተከተለኝ…» የሚሉትን ማኅበረሰብ መናቅና የማሰላሰል አቅሙን መገመት ነው የሚሆነው።

ይህንንም ይዞ፥ የግሩፑን እንቅስቃሴ ጎራ ብሎ የሚመለከት ሰው፥… ግሩፑ ውስጥ ያሉትን እንቅስቃሴዎችና ንቁ የጥላቻ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሰዎች 50 ገደማ ብቻ እንደሆኑ መታዘብ ይቻላል። ለዚያውም በወረዱ ቃላቶች የተቀመሙ ስድቦችንና፣ በሕግም በኅሊናም ፊት በወንጀለኝነት ሊያስጠይቁ የሚችሉ የምስል ቅንብሮችን፥ ተቋቁሞ መቆየት ለቻለ ነው። (በነገራችን ላይ፥ አንድ ግሩፕ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቃላቸውን መመጠንና ራሳቸውን መግራት አለመቻላቸው በራሱ የሚነግረን ትልቅ ነገር አለው።)

እኔ ከግሩፑ ውስጥ በጣም ትልቅ እንቅስቃሴ ተደርጎበት ያየሁት ልጥፍ (post): 249 like፣… 43 comment… እና 0 share ያለው ነው። ምናልባትም ብዙ ሰው ይሳተፋል የሚለውን ስሜት ለመፍጠር ሊሆን ይችላል፥ ይኸው ትልቁ ታይታ የገጠመው ልጥፍ (post) pin ተደርጎ የገባ ሁሉ ከአናት ላይ እንዲያየው ተደርጓል። …በአንፃሩ፥ Teddy Afro መጨረሻ ላይ፥ የሙዚቃ ጉዞውን በተመለከተ የለጠፈው post ላይ ያለውን የወዳጆቹን እንቅስቃሴ ስናየው፥ 895 like, 366 comment እና 110 share አለው።

እንዲህ ያለ የወረደ የሂሳብና የቆጠራ ስሌት ውስጥ የገባሁት፥ ጥላቻን ለመስበክ ወገባቸውን ቋጥረው ላይ ታች የሚሉ፣ ማኅበራዊ ድህረ ገፆች ላይ ሽብር የሚነዙና ሰዎች ድህረ ገፆቹ ላይ በሰከነ መንፈስ እንዲወያዩና እርስበርስ እንዲቀራረፁ የሚያውኩ ወዳጆች ሆይ ሆይታ በከንቱ እንደሆነ ብንገነዘብ ብዬ ነው። ጃዋር ካቅሙ (ከደረሰበት የቀለም ትምህርት ደረጃም አንፃር፥ ግሩፕ ውስጥ ያሉ አባላትን በመቁጠር ደረጃ መውረዱ ገርሞኝ ነው።) በትዊተርና በፌስቡክ ገጾቹ ላይ ቁጭ ብሎ…. የ #boycottbedele ግሩፕ አባላት ብዛት ይኽን ያህል ሆኑ፥ ይኽን ያህል ደረሱ እያለ ማቅራራቱን ታዝቤ  ነው።

ትናንትና Soli S Gmichaelም እንዳለችው ግሩፕ በመሆን ፈንታ #fan_page ቢሆን ኖሮ ግን፥ ሰዎች (ሁሉም ባይሆኑም) መርጠው ስለሚገቡ፥ ዓላማውን ይደግፋሉ/አይደግፉም ብሎ ለመቀወጥ፥ ከግሩፕ የተሻለ አሳማኝ ሊሆን ይችል ነበር። ….ለዚህም እንደ ቀላል ማረጋገጫ፥ እነ አብይ አቶምሳ የከፈቱትን (እንደዛ ያልኩት አብይ ወደዛ ገጽ ከ1ም ሁለት ጊዜ invite አድርጎኝ ስለነበር ነው።) ገጽ የወደዱት (like ያደረጉ) አባላት 2509 ብቻ መሆናቸው ነው። ስለሆነም ሁሉም በማስተዋልና በመገንዘብ ቢሆን ወደፊት እርስበርስ ከመተፋፈር ይጠብቀናል።

የኤትኖግራፈር ተመራማሪውና ፀሐፊው Afendi Muteki ደግሞ በጉዳዩ ላይ እንዲህ ይላል “ወገኖቼ! አንዴ እንረጋጋ፡፡ እኔ የምላችሁን ስሙኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰከን ብላችሁ አስቡ፡፡ ሰዎች ገንዘብና ዝናን እያሰቡ መጠቀሚያ እያደረጓችሁ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ የዚህን ወንጀል ቀንደኛ መሪዎች እናጋልጣለን፡፡ በህዝብ ደም ለመነገድ የሚያደርጉትን ብልጣብልጥነት በትዕግስት አናልፈውም፡፡ አንዳንዶቹ ከላይ ለኦሮሞ የሚቆረቆሩ እያስመሰሉ በድብቅ ግን እራሳቸው “ነፍጠኛ” እያሉ ከሚሰድቧቸው ቡድኖችም ጋር በሚስጢር እንደሚሰሩ ተጨባጭ ማስረጃ አለን፡፡ ወላሂ!! አስቡበት! ረጋ በሉ! በጨዋነት እንነጋገር!” (ሙሉውን ከእርሱ ገፅ አንብቡት።)

ሌሎችም እንዲሁ ነገሩንና ድብቅ አጀንዳውን በግልፅ እንዲረዱት፥ ካመንንበት፥ ሀሳቡን በማጋራት (share በማድረግ) እርስ በርስ እንጠባበቅ።

ነፍስ ኄር ሚካያ በኃይሉ (ከ1969 – 2006 ዓ/ም)

ሚካያ በኃይሉን ከሀሳቤ ልለያት አልቻልኹም። በየመሀሉ ገጭ ትልብኛለች። …አንዠቴን በላችው። 15001_103357143037030_6673039_nከተፈጥሮ ጋር አጋጨችኝ። ከእምነት ጋር አፋጨችኝ። ቆሞ ከመሄድ ጋር አቃቃረችኝ። ተጠራጣሪነቴን አበዛችው። ከንቱነትን ለሌላ ብዙኛ ጊዜ አስተማረችኝ። ‘በቃ ለዚሁ ነው ይኽ ሁሉ መባከን? ይህ ሁሉ መበላለጥ? ይህ ሁሉ መገጫጨት? ይህ ሁሉ መባላት? ይህ ሁ… ሉ መሆን? ’ አሰኘችኝ። በጣም እወዳት ነበር። በጣም ማለት፥ በጣም። …በጣም ማለት፥ እንደ ሙዚቃ ወዳጅና እንደ ሙዚቀኛ አክባሪ። አልበሟ ለእኔ ብቻ የወጣ ነበር የሚመስለኝ። …ይህ ሲሰማኝ ረከሰብኝ። በጣም ረከሰብኝ። …ማለት፥ ዋጋው ረከሰብኝ።

ይሄን ሁሉ ዓለም የያዘ አልበም በዚህች ትንሽ ብር ብቻ? ይሄን ሁሉ የሙዚቃ ድግስ በዚህች ሚጢጢዬ ዲስክ አጮልቆ መታደም? ወይ ጉድ፥ ፈጣሪ የእጁ ሥራ ልዩ! …ብዬ፥ ሙዚቃ ሲቀረፅ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ሁሉ እንዳዲስ ስገረም…. እንደልጅ ስቦርቅና ስደሳሰት…. ከዚያ ለቡዳውም ለመጋኛውም፣ ለብሶቱም ለደስታውም፣ ለእሮሮውም ለእንጉርጉሮውም፣ ለመተኛውም ለመንቂያውም፣ ለዘመዱም ለወዳጁም፣ ለክፉውም ለደጉም… ብዬ፥ ፌጦ ይመስል በርከት አድርጎ መሸከፍ እያሰኘኝ ብቻዬን ስስቅ። …ከራሴ ጋር ሲያጣላኝ።

(ይህ ስሜቴ ‘cliche’ ነው መሰለኝ። ብዙ የድሮ ሙዚቃዎችን ስሰማ፥ የትዕግስት (ኒኒ)ን አልበም ስገዛ፣ የጂጂን ሙዚቃዎች በሰማሁ ቁጥር፣ የዘሪቱን፣ የሚካኤልን፣ የቴዲ ጃ ያስተሰርያልን፣ የኢዮብን…. ሌላም ሌላም፥ ልዩነታቸው በስሜት መረቤ ልኬት ብቻ ተወስኖ፤ የሙዚቃ ባህር ላይ ከሚታዩ መደበኛ ዓሶች መካከል በሆነ ዓይነት የጣዕም ልዩነት ብቅ የሚሉ ልዩ ዓሶችን ስመለከት… ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሯን እንደተሳመች ኮረዳ ጭውውው ይልብኛል።)

…ለነገሩ ስወድ እንዲህ ነኝ። ስደመም እብድ ነኝ። የሆነው ሁሉ ለእኔ ብቻ የሆነ ይመስለኝና እፍነከነካለሁ። ገራገሯን ሚካያ መጀመሪያ ያወቅዃት ሁለት ነጠላ ዜማዎቿን በለቀቀች ሰሞን አለቤሾው ላይ ከአለባቸው ተካ ጋር በነበራት የጨዋታ ጊዜ ነበር። “ሸማመተው”ም አንድ ማስተር ቅጂ ብቻ ኖሮት እርሱም እኔ ጋር ብቻ እንደሆነ እያሰብኹኝ ልቤን አሳብጥ ነበር። ሰው ቢያውቅልኝም ባያውቅልኝም፥ ለራሴ የሆነ ከፍታ ላይ እሆናለሁ። ሰው እንዳይታዘበኝ፥ “ሞኙ” ብሎ እንዳይስቅብኝ ብዬ፥ አስብና ‘የርሱንስ ማን አየ?’ ብዬ የስሜቴን የጋራነት በመገመት መለስ እላለሁ።

ሻካራ ድምጿ ከእርጋታዋ ጋር ተደምሮ፥ አስተያየትና ፈገግታዋ የቤተሰብ ይመስሉና፥ በጆሮዬ መጥታ የምታንሾካሹክልኝ እንጂ ማጫወቻ ውስጥ ከትቼ የምሰማው አይመስለኝም ነበር። በዚያም ላይ አፏ ሲኮለታተፍ ወደ ውስጥ የሚቀሩ ግጥሞችን ለመስማት አደርግ የነበረው ትግልም ሌላ መሳጭ ትዕይንት ነበረ። (ሙዚቃው ላይ ቢያናድደኝም፥ በኋላ ግን በሰጠቻቸው ቃለ መጠይቆች ላይ የእውነትም የሚኮላተፍ ነገር እንዳላት ተረድቼ ትቼዋለሁ)

…እንዲህ ያለ አቅም ኖሯት ደፋር ብትሆን ኖሮ ግን አንድ አልበም ብቻ አበርክታ ታቆም ነበር? ወይስ ስንፍና ነው? – በተለይ እንደሌለች ሳስብ ራሴን እጠይቃለሁ። ከትምህርት ዓለም በ995 ብር (ሳይቆራረጥ) የወር ደመወዝ በዩኒቨርስቲ ረዳት ምሩቅነት፥ ራስን ወደ መቻያ የሥራ ዓለም በተሸጋገርኹበት ዓመት ውስጥ የወጣው አልበሟ ብዙ እቃ ላልነበራት 1ክፍል የኪራይ ቤቴ ሲሳይ ነበረች።

ይድረስ ለማስብህ ለማልምህ ላንተ
ፍቅርህን ለማግኘት ልቤ ከዘመተ፥…

የሚለውን ሙዚቃ ስሰማ፥ ሲሻኝ በቁሙ፣ ሲሻኝ ደግሞ የተዘፈነበትን ፆታ ለራሴ ቀይሬ “ይድረስ ለማስብሽ” ብዬ አብሬያት ጮኽ ብዬ እዘፍን ነበር። …ወጣቷ አከራዬ መጥታ “ጆኒ ዛሬ ደግሞ ተነስቶብሀል” ብላ እስክታናጥበኝ ድረስ ደጋግሜ። …ለነገሩ መጥታም እንደዚያ ብላኝም ሙዚቃው ይቀጥላል። ጩኸቱ ይቀንሳል እንጂ በሀሳብ ነጉዶ ማጉተምተሙ አይቀርም። አከራዬም አልጋዬ ጫፍ ላይ ቁጭ ብላ በራሷ ዓለም ትነጉዳለች።

ጉድለቴ ባፈጠጠበትና ማማረሬ በዝቶ መሸሸጊያ ለውጥ እፈልግ በነበረበት ወቅት ሳይቀር…

ሞላልኝ፣ ሆነልኝ፣ ተሳካልኝ
ልቤ ረካ፥ መጨረሻውን አይቶ
እቅዱን አሳክቶ…

የሚለው ዜማ ልክክ ያለ ታዛ ሆኖ ደብቆኝ ያውቃል። “አይ ይሄ ሀሳቡ ከእኔ ጋር አይሄድም” ብዬ አልተውኩትም። የምሩን ቢሞላ እንደምሆንበት …ሽሽግ፣ ሽጉጥ፣ ድብቅ ብዬበት “ሞላልኝ” ብዬ በጎዶሎ አብጃለሁ። ወላ ዛሬም ድረስ የሚካያን አልበም ማዳመጥ ስፈልግ የምጀምረው ከ4ኛው ትራክ ነው። 4ኛው ትራክ ሞላልኝ ነው። …ሙዚቃ ውበቱ ይሄ ነው። ዓለም አቀፋዊ ቋንቋነቱም ሙላቱም እንዲህ ባለ ጊዜያት ይገለጣል መሰለኝ። ኦ ሚካያ!

ይቀኝልኝ ነፍስህ ለነፍሴ ዝማሬ
እድሜዬን ለካሁት በፍቅርህ ጅማሬ።

የሚለውን ሙዚቃ፥ ቀልቤን ሰብስቤ …ሰበቤ ብዬበታለሁ። ባለቤት በሌለበት እሪሪሪ ብዬ ከነስሜቱ ከንፌበታለሁ። ወላ የሰማሁት ዕለት፥ በኋላ የሆነውን ዓይነት ክሊፕ በቀልቤ ስዬ ጠፍቼ ነበር። እውነቴን ነው።

ውዴ የኔ ነህ፥ ለነጠላ ነፍሴ ተድላን እየሞላህ
ፍቅሬ ላንተ ነው እንደፀሐይ ጨረቃ ዘመኔን ላሰላህ

ብላ ከፍታ ስትወጣ፥ እኔም ፊቴን ቁጥር አድርጌ እጆቼን ዘርግቼ፣ በስሜት፥ ውዴን በመናፈቅ ተከትያታለሁ። ፍቅር አልበረክት ባለኝ ጭጋጋማ ወቅት እንኳን “ውዴ ሆነልን ብራ ቀን፥ ወረት እንደሰማይ የራቀን” ብዬ እሪሪ ብያለሁ። ሙዚቃ ነዋ!

አበባ የመሳሰሉ፥ ቀንበጥ ልጆችን ተመልክቼ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ፤… ከወዲህ ክብር ጥበቃና ይሉኝታ፣ 24206_103543823018362_1756953_nከወዲያ ውበትና አስገዳጅ ቁመና እየፈተኑኝ እንደሁኔታው መስመር በመተላለፍ ለዚያችው ቅፅበት ባላለፈ ጨዋታ የሰው ቆንጆ ሳሽኮረምም፥… ወይ ደግሞ እንኳን ቁንጅናቸውን ፆታቸውን እንኳን ከቁብ በማልዶልበት አጣዳፊ ማኅበራዊ ወቅቶች (ለምሳሌ፥ ቦታ ጠፍቶ አቅጣጫ እንደመጠየቅ፣ ወይ ለስራ ጉዳይ በሚደረግ ውይይት ውስጥ) ሴቶቹ ታየሁ ተለከፍኹ ብለው ሲንቀባረሩ (በነገራችን ላይ ሲያናድዱኝ!) ሁኔታቸውን ከተገነዘብኹ፥…

የማነህ ቀብራራ የጌታ ልጅ መሳይ
ለሌላ እንዳይመስልህ አንተን ቆሜ ሳይህ

የሚለው ሙዚቃ ፆታው ተገልብጦ እንጂ ሌላ ምን ውልብ ሊልብኝ?

ድንገት ሲቀናኝ… ጀግና ማረኹኝ
ያ ባተሌ ያ ቆፍጣና
የስራ ሰው ያ ሳተና
ለኑሮው ሲል ደፋ ቀና
ላይ ታች ሲል ቤት ሊያቀና
ሲክብ ባየው ወደድኹት…

ስትል አብሬያት ተደምሜ፥ በፍቅር የመዘንዃቸውና የቀለሉብኝ፣ ሞላልኝ ስል የጎደሉብኝን፥… የእኔንም ልኬት – መመዘን መቅለሌን – በነሱ ዓይን ለመገመት እያሰብኹ፥ ‘ተሸውዳለች’ እያልኹ፤ ‘አመለጠችኝ’ እያልኹ፤ ‘እሷስ ምን ትል ይሆን?’ እያልኹ፥ ከራሴ ጋር ተጫውቼባቸዋለሁ።

በሰጠኸው ፍቅር፣ ልቤ ተቀማጥሎ
ሹመት ንግስናህን አላውቅበት ብሎ
ጠግቦ ጌትነቱን አልችል ብሎ
ሄደ ክብሩን ጥሎ፥ ከቤትህ ኮብልሎ…

ብላ በቁጭት እሮሮዋን ስታሰማና ዞሬ መጣሁ ስትል፥ ጨምላቅነቷን እየታዘብኹ፣ ትህትናና እምነቷን እያደነቅኹኝ፣ የጌታዋን ጌትነት እየሳልኹ …አብሬያት በሀሳብ አቀርቅሬ አንጎርጉሬያለሁ። ከዚያ በኋላ ያለውንም አስቤው ከራሴ ጋር ተጫውቻለሁ። በርሱ በኩል ሾልኬ የራሴን ጉዳዮች ጎልጉያለሁ።

ደለለኝ ደለለኝ ደለለኝ
ማሬ ነሽ ብሎ አታለለኝ
ወተቴ እያለ ሸነገለኝ
ቅቤ ምላስህ ገደለኝ።…

የሚለውን ሙዚቃ ስሰማ እቆምና፥ እግሬ መሬቱን በስልት እየረገጥኹ፣ ክሊፑን እንደሚሰራ ሰው በለስላሳ ውዝዋዜ ታጅቤ ጨሼበታለሁ። በንፅፅሩ ውበት ተደምሜያለሁ። ሰማይና ምድር የእኔ ግዛቶች የሚመስሉኝ ጊዜም ትዝ አለኝ። ወላ ክለብ ውስጥ ዲጄውን ባይኔ ተለማምጬ ደለለኝን ያስከፈትኹበት ጊዜ ብዙ ነው።

የሰው ስጋ እርም ነው ብሎ ያለው
እኔስ ልበላህ ነው በቃ ማበዴ ነው
ሰው በልተሻል የሚከሰኝ ማነው?
ምበላህ ምውጥህ ስሜ ባልጠግብህ ነው።

የሚለውን ስሰማ ደስ ይለኝና፥ ድንገት ሳቅ ያፍነኛል። ፈገግ ብዬ ነው የምጨርሰው። ትዕይንቱ ማርኮኝ ‘ና ትብላህ’ እያልኹ አብሬ እየጠራሁት። …ደግሞ ከወዲህ ውዴን ሳስብ ነይ እያልኹኝ። “የዛሬን እንጫወት የነገን አናውቅም፤ አትሰስቺው ፍቅርሽን ግድ የለሽም አያልቅም።” እያልኹ እየጎተትዃት። ስበላት ስሰለቅጣት እየታየኝ፥ ዘግንኖኝ ሳማትብ። ደግሞ በብልሀት ስቀረጥፋት። በዓይኔ በቀልቤ ስውጣት። ዓለሜን ቀይሬ በራሴ ዓለም ሳብድ። ያበድኹባቸውን ዓለሞች በዓይነ ህሊናዬ ስቃኝ ።

ያንተ መሆኑ እፈልጋለሁ
ግን እፈራሀለሁ።
የልብ እምነትና የሴት ልጅ ክብር
መተኪያ የለውም አንዴ ቢሰበር
እቀርብህና ደግሞ ይርቅሀል
ልቤ ይጨነቃል።
ድብቅ ነሽ ትላለህ ልቤን ባታገኘው
ልቤን ያገኘህ እለት ቅስሜንስ ብትሰብረው?

እያለች ስጋቷንና ጉጉቷን በጋራ፥ በአያዎ ዘይቤ፥ ልሂድ ወይስ ልቅር ዓይነት እያለች ግራ ስትጋባ። …ደግሞ ተረዳኝ ብላ ስትማፀነው። ደግሞ ሌላ ዓይነት የመወደድ ፍርጃ ስታሳየኝ። …እንዲሁ አብሬያት እንከራተታለሁ።

በሌሎቹ ሙዚቃዎቿም ብዙ! ድጋሚ ስሰማቸው ድጋሚ እየወደድዃቸው፤ ድጋሚ ስሰማቸው ድጋሚ እየናፈቅዃቸው ፈታ የምልባቸው አጃቢዎቼ። …ስሰማቸው ባለሁበት ሆኜ በስልት ልቤ ይናጣል። ሰውነቴ በስሜት ይንቀሳቀሳል። …ነጠላ ዜማዎቿም አሟቂ ጋቢዎቼ ነበሩ። ሕይወት ይቀጥላል! ልዩነቱ ሌላ አዲስ ሙዚቃ አታመጣም እንጂ፥ ሚካያ ወደፊትም በሥራዎቿ ከእኔ ጋር ነች።

ነፍስ ኄር MICAIAH BEHAILU ! ኦ ድምፅ! ኦ ብስለት! ኦ ልዩነት! ኦ ግጥም! ኦ አተያይ! ኦ ዜማ! ኦ እርጋታ!…ኦ ሚካያ!

Follow

Get every new post delivered to your Inbox.

Join 51 other followers